እስራኤል ሁለቱን የኮንግረስ አባላት ወደ ሃገሯ እንዳይገቡ አገደች

ኮንግረስ አባላት የሆኑት ራሺድ ተሊብ እና ኢልሃን ኦማርን Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ ኮንግረስ አባላት የሆኑት ራሺድ ተሊብ እና ኢልሃን ኦማርን

የአሜሪካ ኮንግረስ አባላት የሆኑት ራሺድ ተሊብ እና ኢልሃን ኦማርን ወደ እስራኤል እንዳይገቡ እገዳ ተጣለባቸው።

የእስራኤል ባለስልጣናት ከዚህ ውሳኔ የደረሱት ሁለቱ የኮንግረስ አባላት ከዚህ ቀደም እስራኤል የፍልስጤማውያንን ጥያቄ የምታስተናግድበትን አግባብ በተደጋጋሚ በመኮነናቸው ነው ተብሏል።

ፕሬዝደንት ትራምፕ የእስራኤል መንግሥት በእነዚህ ሙስሊም የኮንግረስ አባላት ላይ ይህን መሰል ውሳኔን እንዲያስተላልፍ ከፍተኛ ጫና ሲያሳድሩ ነበር።

ፕሬዝደንት ትራምፕ ራሺድ ተሊብ እና ኢልሃን ኦማርን ጨምሮ ከሌሎች ሁለት የኮንግረስ አባላት ጋር የቃላት ጦርነት ውስጥ መግባታቸው ይታወሳል።

ሁለቱ የኮንግረስ አባላት ከፊታችን እሁድ ጀምሮ በእስራኤል እና በፊልስጤም ግዛቶች ጉብኝት ለማድረግ ቀነ ቀጠሮ ይዘው ነበር።

ይህ የእስራኤል ውሳኔ ይፋ ከመደረጉ በፊት ትራምፕ በትዊተር ገጻቸው ላይ የኮንግረስ አባላቱ እስራኤልን እንዲጎበኙ የሚፈቀድ ከሆነ "ትልቅ ድክመትን ያሳያል። ራሺድ ተሊብ እና ኢልሃን ኦማር እስራኤልን እና አይሁድን ይጠላሉ። ምንም ነገር ቢደረግ ይህን አመለካከታቸውን መቀየር አይቻልም" ሲሉ አስፍረው ነበር።

ከእስራሴሉ ጠቅላይ ሚንስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ ጋር የቅርብ ግነኙነት ያላቸው ትራምፕ፤ የምክር ቤቱ አባላት በእስራኤል ተቀባይነት የሌላቸው ሰዎች ለማድረግ ከፍተኛ ጥረትን ሲያደረጉ ቆይተዋል። ከዚህ በተጨማሪም ከኮንግረስ አባላቱ ጋር የቃላት ጦርነት ውስጥ የገቡት ትራምፕ "ዘረኝነት የተሞላበት" በተባለው ነቀፋቸው የኮንግረስ አባላቱ "ወደ መጣችሁበት ወደ ወላጆቻችሁ አገር ተመለሱ" ሲሉ ነቅፈዋቸዋል።

ከአንድ ወር በፊት በአሜሪካ የእስራኤል አምባሳደር የኮንግረስ አባላቱ እስራኤል እንዲገቡ እንደሚፈቀድ አሳውቀው ነበር። በወቅቱ አምባሳደሩ "ለአሜሪካ ኮንግረስ ካለን አክብሮት እና የሁለቱን ሃገራት ጠንካራ ግነኙነት ከግምት ውስጥ በማስገባት" ሁለቱ ዲሞክራቶች እስራኤል እንዲገቡ ይፈቀድላቸዋል ብለው ነበር።

ይሁን እንጂ የእስራኤል የሃገር ውስጥ ሚንስቴር "እስራኤልን ለመጉዳት የሚያስቡ ወደ ሃገሪቱ እንዲገቡ ይፈቀድላቸዋል ብሎ ማሰብ አይቻልም" በማለት ሁለቱ የኮንግረስ አባላት ወደ እስራኤል መጓዝ እንደማይችሉ አስታውቋል።

የአሜሪካ መገናኛ ብዙሃን እንደዘገቡት ከሆነ የኮንግረስ አባላቱ ወደ እስራኤል ለመሄድ ያቀዱት የፊታችን እሁድ ነበር። በእስራኤል ቆይታቸውም ፍልስጤማውያን እና እስራኤላውያን የይገባኛል ጥያቄ የሚያነሱባቸውን መንፈሳዊ ቦታዎችን ለመጎብነት ቀጠሮ ይዘው ነበር።

ራሺድ ተሊብ በፍልስጤም መንደር ውስጥ የሚኖሩትን ሴት አያታቸውን ለመጎብኘትም አቅደው ነበር።

እስራኤል ከዚህ ውሳኔ ከመድረሷ በፊት ጠቅላይ ሚንስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ ከሃገር ውስጥ ሚንስቴር ሚንስትር፣ ከደህንነት አማካሪያቸው እና ከጠቅላይ አቃቤ ሕጉ ጋር ውይይት ማድረጋቸውን ሃሬትዝ የተሰኘው የእስራኤል ጋዜጣ ዘግቧል።

ከዚህ ቀደም እስራኤል ከብሄራዊ ደህንነቷ፣ ከምጣኔ ሃብቷ፣ ከባህል እና ከትምህርት ፍላጎቷቸ ጋር የሚነጻጸር አድማ ያደረገ ወደ እስራኤል እንዳይገባ ትከለክላለች።