ግብጽ ውስጥ አንድ የኤድስ ህመምተኛ በግድ ከሆስፒታል መውጣቱ ቁጣ ቀሰቀሰ

የኤድስ ህመምተኛው በግድ ተጎትቶ ሲወጣ Image copyright Source: Social media

ኤችአይቪ በደሙ ውስጥ ያለ ግለሰብ ረቡዕ እለት በግድ ከሆስፒታል እንዲወጣ ሲደረግ የሚያሳይ ምስል ከታየ ኋላ የተቀሰቀሰ ቁጣን ተከትሎ የግብጽ ባለሥልጣናት በጉዳዩ ላይ ምርመራ መጀመራቸው ተገለጸ።

ከዋና ከተማዋ ካይሮ 100 ኪሎ ሜትር ርቆ በሚገኘውና ጋርቢያ ተብሎ በሚታወቀው የግብጽ ሰሜናዊ ክልል ውስጥ ባለ ካፍር ኤል ዛያት በተባለ ሆስፒታል ውስጥ ህመምተኛው መሬት ላይ በኃይል እየተጎተተ እንዲወጣ ሲደረግ የሚያሳየው ቪዲዮ በርካታ ሰዎችን አስቆጥቷል።

በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ በስፋት የተሰራጨውን ቪዲዮን ተከትሎ የመንግሥት ባለሥልጣናት አስፈላጊውን ምርመራ እንደሚያደርጉ አሳውቀዋል።

የኤድስ ወረርሽኝ በኢትዮጵያ

የግብጽ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር፤ ድርጊቱን የፈጸሙት የሆስፒታሉ ሠራተኞች ለህመምተኛው ተገቢ አገልግሎት ባለመስጠት ተጠያቂ እንደሚደረጉም አሳውቋል።

ስማቸው ያልተጠቀሰ አንድ የሆስፒታሉ ከፍተኛ ኃላፊ እንዳሉት ግን የኤድስ ህመምተኛ የሆነው ግለሰብ ወደ ሆስፒታሉ ሲመጣ አደንዛዥ ዕፅ ተጠቅሞ እንደነበር ተናግረዋል።

እንግሊዛዊው ከኤችአይቪ 'ነጻ' ሆነ

ኮንዶም መጠቀም እያቆምን ይሆን?

ስለክስተቱ በስፋት ከተነገረ በኋላ የአገሪቱ ብሔራዊ ኤችአይቪ/ኤድስ ፕሮግራም ኃላፊዎች ወደ ሆስፒታሉ ሄደው ህመምተኛውን ለማግኘት ቢሞክሩም ሊያገኙት አልቻሉም።

ኃላፊዎቹ ከሆስፒታሉ በግድ እንዲወጣ የተደረገውን ግለሰብ በማግኘት ለኤድስ ህሙማን ብቻ ህክምና ወደሚደረግበት ሆስፒታል እንዲገባና አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያገኝ ጥረት እያደረጉ ነው።

በግብጽ ውስጥ የሚገኙ የኤችአይቪ ኤድስ ህሙማን ከፍተኛ የሆነ መገለል እንደሚደርስባቸው ይነገራል።

ተያያዥ ርዕሶች